አንበሳ (Panthera leo) ጡት አጥቢ የእንስሶች መደብ ውስጥ Felidae ተብሎ የሚታወቀው ቤተሰብ አባል ሲሆን ግዙፍ ድመቶች ከሚባሉት 4 አራዊት አንዱ ነው። ከነዚህም መካከል ነብር ከሚባለው ግሥላ መሳይ አውሬ ቀጥሎ በቁመቱና ክብደቱ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። አንበሳ ዛሬ በአፍሪካ (ከነኢትዮጵያ) እና በህንድ ብቻ የሚገኝ ሲሆን በታሪክ እስያና በደቡብ አውሮፓ እንደነበርና እንደጠፋ ይታወቃል።
አንበሶች በጣም ቁጡ ሊሆኑ ይችላሉ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የሙጭሊትን ያህል ገራምና ተጫዋች ይሆናሉ። ሲጠግቡ በዝግታ የሚያንኮራፉ ቢሆንም እንኳ እስከ ስምንት ኪሎ ሜትር ድረስ ሊሰማ በሚችል ኃይለኛ ድምፅ ሊያገሡ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ሰነፎችና ልፍስፍሶች ይመስሉ ይሆናል፤ ሆኖም በሚያስገርም ፍጥነት የመንቀሳቀስ ችሎታ አላቸው። የሰው ልጅ፣ አንበሳ ባለው ድፍረት ለዘላለም ሲወሳ እንዲኖር አድርጓል፤ በመሆኑም ደፋር ሰው አንበሳ ተብሎ ይጠራል። [2]
አንበሶች በማኅበር ከሚኖሩት የድመት ወገን የሆኑ እንስሶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በትልልቅ መንጋ ተከፋፍለው የሚኖሩ ሲሆን እያንዳንዱ መንጋ ከጥቂት አባሎች አንስቶ ከ30 በላይ ሊደርስ ይችላል። አንድ መንጋ የጠበቀ ዝምድና ያላቸው በርከት ያሉ ሴት አንበሶች ይኖሩታል። አንድ ላይ ይኖራሉ፣ ያድናሉ እንዲሁም ይወልዳሉ። ዕድሜ ልካቸውን ሊዘልቅ የሚችለው ይህ የጠበቀ ትስስር ለመንጋው ጠንካራ መሠረት የሚጥል ከመሆኑም በላይ ለመንጋው ሕልውና ጥሩ ዋስትና ይሆናል። [3]
እያንዳንዱ መንጋ እየተዘዋወሩ የሚጠብቁና የመንጋውን የክልል ወሰን የሚያወጡ አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ለአካለ መጠን የደረሱ ወንድ አንበሶች ይኖሩታል። እነዚህ ዕጹብ ድንቅ የሆኑ አውሬዎች ከጥቁሩ የአፍንጫቸው ጫፍ አንስቶ እስከ ጭራቸው ጫፍ ድረስ ከሦስት ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው ሲሆን ከ225 ኪሎ ግራም በላይ ሊመዝኑ ይችላሉ። ቤተሰቡን በበላይነት የሚቆጣጠሩት ወንዶቹ ቢሆኑም አመራር የሚሰጡት ግን ሴቶቹ ናቸው። ወደ ጥላ ሥፍራ መሄድን ወይም አደን መጀመርን በመሳሰሉት ሁኔታዎች ብዙውን ጊዜ መንጋውን ለአንድ ዓይነት እንቅስቃሴ የሚያነሳሱት ሴቶቹ አንበሶች ናቸው።[4]
ሴት አንበሶች በአብዛኛው በየሁለት ዓመቱ ይወልዳሉ። ግልገሎቹ በሚወለዱበት ጊዜ ምንም ዓይነት አቅም አይኖራቸውም። ግልገሎችን ማሳደግ የሁሉም የጋራ ሥራ ነው፤ በመሆኑም ሴቶቹ አንበሶች በሙሉ በመንጋው ውስጥ ያሉትን ግልገሎች ይጠብቃሉ እንዲሁም ያጠባሉ። የግልገሎቹ ዕድገት ፈጣን ሲሆን በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ መሮጥና መቦረቅ ይጀምራሉ። ልክ እንደ ሙጭሊቶች እየተንደባለሉ ይጫወታሉ፤ ከሚያጫውቷቸው ጋር ይታገላሉ፤ እንዲሁም በረጃጅሙ ሣር ውስጥ ወዲያና ወዲህ ይዘላሉ። እያንዳንዱ የሚንቀሳቀስ ነገር ሁሉ ስሜታቸውን ይማርከዋል፤ ቢራቢሮዎችን ለመያዝ ይዘላሉ፣ ትናንሽ ነፍሳትን ያሳድዳሉ፣ ከየጭራሮና ከየሐረጉ ጋር ይታገላሉ። ይበልጥ ስሜታቸውን የሚማርከው ግን እነርሱን ለማጫወት እናታቸው ወዲያና ወዲህ የምታወናጭፈው ጭራዋ ነው። [5]
እያንዳንዱ መንጋ የሚኖርበት በደንብ የተከለለ ቦታ ያለው ሲሆን ይህ መኖሪያ ብዙ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ሊኖረው ይችላል። አንበሶች ውኃ እንደ ልብ ባለበትና ከቀትር ሐሩር የሚከላከል ጥላ በሚያገኙበት ከፍ ያለ ቦታ ላይ መኖር ይመርጣሉ። በእንዲህ ዓይነቱ ሥፍራ ከዝሆኖች፣ ከቀጭኔዎች፣ ከጎሽና ከሌሎች ሜዳማ በሆኑ ሥፍራዎች ከሚኖሩ እንስሶች ጋር በአንድነት ይኖራሉ። አንበሳ አብዛኛውን ጊዜውን በእንቅልፍ ጥቂቱን ጊዜ ደግሞ በአደንና በተዋስቦ ያሳልፋል። እንዲያውም አንበሶች በቀን ውስጥ ወደ 20 የሚጠጋውን ሰዓት የሚያሳልፉት በዕረፍት፣ በመተኛት ወይም በመቀመጥ ነው። ከባድ እንቅልፍ ተኝተው ሲታዩ ሰላማዊና ለማዳ ይመስላሉ። ይሁን እንጂ በዚህ መታለል የለብህም፤ አንበሳ እጅግ ቁጡ ከሆኑት አራዊት መካከል አንዱ ነው![6]
አንበሶች በጣም ቀልጣፋና ፈጣን ቢሆኑም እንኳ በአደን ጊዜ የሚሳካላቸው 30 በመቶ ብቻ ነው። በመሆኑም አንበሶች ከተደቀኑባቸው ትልልቅ አደጋዎች አንዱ ረኃብ ነው።
ለአካለ መጠን የደረሰ አንድ አንበሳ ያለው ጥንካሬ እጅግ የሚያስገርም ነው። በቤተሰብ ደረጃ የሚያድኑ እንደ መሆናቸው መጠን ከ1,300 ኪሎ ግራም በላይ ክብደት ያላቸውን እንስሳት የመጣልና የመግደል አቅም እንዳላቸው ይነገራል። አንበሶች በመጀመሪያ ላይ በሰዓት እስከ 59 ኪሎ ሜትር ድረስ ሊሮጡ ይችላሉ፤ ሆኖም ይህ ፍጥነታቸው እስከ መጨረሻ አይዘልቅም። በዚህ ምክንያት ቀለባቸውን ለማግኘት አድብቶ የመያዝ ዘዴ ይጠቀማሉ። የማደኑን ተግባር 90 በመቶ የሚያከናውኑት ሴቶቹ አንበሶች ቢሆኑም በሚበሉበት ጊዜ ትልቁን ድርሻ የሚያገኙት ትልልቆቹ ወንድ አንበሶች ናቸው። አደን በሚጠፋበት ጊዜ አንዳንዴ አንበሶች በጣም ስለሚርባቸው ያገኙትን መብል ለራሳቸው ግልገሎች እንኳ ለማካፈል ፈቃደኛ አይሆኑም። [7]
ከብዙ ዓመታት በፊት ባለ ግርማ ሞገሱ አንበሳ በመላው የአፍሪካ አህጉር እንዲሁም በእስያ፣ በአውሮፓ፣ በህንድና በፍልስጤም አንዳንድ ቦታዎች ይገኝ ነበር። አዳኝ እንደመሆኑ መጠን ሰውን እየተቀናቀነ የሚኖር እንስሳ ነው። በከብቶች ላይ አደጋ የሚጥልና በሰዎች ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ አንበሳ ገና እንደታየ በጥይት የሚገደል ፍጡር ሆነ። የሕዝብ ቁጥር ፍንዳታ የአንበሳን መኖሪያ በእጅጉ አመናምኖታል። ዛሬ ከአፍሪካ ውጪ ባለው የዓለም ክፍል በዱር የሚኖሩት አንበሶች በጥቂት መቶዎች ብቻ የሚቆጠሩ ሆነዋል። በአሁኑ ጊዜ አንበሶች ሰው ከሚያደርስባቸው ጥቃት ሙሉ በሙሉ ተጠብቀው መኖር የሚችሉት ጥበቃ በሚደረግባቸው ክልሎች ውስጥና በዱር አራዊት መጠበቂያ ቦታዎች ብቻ ሆኗል። [8]
አንበሶች በሚያገሡበት ጊዜ በብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ሊሰማ የሚችል ከፍተኛ ድምፅ የማውጣት ልዩ ችሎታ አላቸው። አንበሳ ሲያገሣ የሚያሰማው ድምፅ “እጅግ ማራኪ ከሆኑት የተፈጥሮ ድምፆች” አንዱ እንደሆነ ይነገራል። ብዙውን ጊዜ አንበሶች በጨለማ ሰዓትና ንጋት ላይ ያገሣሉ። ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ አንበሶች የሚያገሡ ሲሆን አንዳንዴም የመንጋው አባላት በአንድነት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያገሣሉ።
በአንበሶች ላይ ጥናት የሚያካሂዱ ሳይንቲስቶች አንበሶች የሚያገሡባቸው የተወሰኑ ምክንያቶች እንዳሉ ይናገራሉ። ወንዶቹ አንበሶች የሚኖሩበትን ክልል ድንበር ለማሳወቅ እንዲሁም ሌሎች ወንድ አንበሶች ወደ ክልላቸው እንዳይገቡ ለማስጠንቀቅ ሲሉ ያገሣሉ።
በርቀት ወይም በጨለማ ተነጣጥለው ያሉ የአንድ መንጋ አባላት ያሉበትን ቦታ ለመጠቆም ያገሣሉ። በተጨማሪም አንድ እንስሳ ከገደሉ በኋላ ለሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት ምግቡ ያለበትን ቦታ ለማሳወቅ ያገሣሉ።
አንበሶች በሚያድኑበት ጊዜ የሚያድኗቸውን እንስሳት ለማስደንበር ብለው አያገሡም። ሪቻርድ ኤስቲዝ ዘ ቢሄቭየር ጋይድ ቱ አፍሪካን ማማልስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “አንበሶች የሚያድኑትን እንስሳ ለማጥመድ ሲሉ ሆን ብለው እንደሚያገሡ የሚጠቁም ምንም ነገር የለም (በተሞክሮዬ እንዳየሁት በአንበሳ የሚታደኑ እንስሳት አንበሳ ለሚያሰማው የግሣት ድምፅ ብዙም ትኩረት አይሰጡም)።” [9]
ሲምባ በስዋሂሊ “አንበሳ” ማለት ነው። [10]